የሀገር ውስጥ ዜና

የደቡብ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከ8 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

By Melaku Gedif

February 12, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሥድሥት ወራት ከ8 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የደቡብ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ ይግለጡ ሃምዛ ÷ በግማሽ ዓመቱ ከመደበኛ ግብር ከፋዮች እና መዘጋጃ ቤት አገልግሎት 9 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

የታቀደውን እቅድ በስኬት ለማጠናቀቅም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ከማከናወን ባለፈ ቀልጣፋ አሰራሮችን በመዘርጋት በቅንጅት መሰራቱን አብራርተዋል፡፡

ባለፉት ሥድሥት ወራትም 8 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻን ነው አቶ ይግለጡ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡

በዚህም የእቅዱን 96 ነጥብ 9 በመቶ ማሳካት መቻሉን የጠቆሙት ሃላፊው÷ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው አንስተዋል፡፡

ገቢው ከ188 ሺህ በላይ ከሆኑ የመደበኛ ግብር ከፋዮች እና መዘጋጃ ቤት አገልግሎት የተገኘ መሆኑን አቶ ይግለጡ ጠቁመዋል፡፡

ደረሰኝ የማይከፍሉ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ህጋዊ መስመሩን ተከትለው እንዲሰሩ ቢሮው የተለያዩ እርምጃዎችን እንደወሰደም አብራርተዋል፡፡

በቀጣይ ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ እንዲከፍሉ አስፈላጊውን ቅስቀሳ እና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል፡፡

 

በመላኩ ገድፍ