ከደረጃ በታች የሆኑ ከ1 ሺህ 86 ሜትሪክ ቶን በላይ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጓል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግማሽ ዓመቱ 1 ሺህ 86 ነጥብ ሜትሪክ ቶን የተለያዩ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ማገዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የ4 ሺህ 349 አስመጪዎችን ጥያቄ በመቀበል ከ1 ሚሊየን 86 ሺህ በላይ ሜትሪክ ቶን አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ በወጣላቸው የገቢ ምርቶች ላይ የኢንስፔክሽን ሥራ ለማከናወን ታቅዶ÷ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ሜትሪክ ቶን የገቢ እቃዎች ላይ የኢንስፔክሽን ሥራ መከናወኑ ተገልጿል፡፡
የላቦራቶሪ ፍተሻ እና ኢንስፔክሽን ሥራዎች የተከናወኑትም የተለያየ መጠን ባላቸው÷ የምግብ ዘይት፣ ሩዝ እና የስንዴ ዱቄት ላይ መሆኑን በሚኒስቴሩ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢያሱ ስምዖን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የተለያየ መጠን ያላቸው÷ ኤል ኢ ዲ አምፖል፣ የኤሌክትሪክ ገመድ፣ ሶላር ቴክኖሎጂ፣ የኃይል አባዥ አምፖል፣ የውኃ ሆዝ፣ የቆርቆሮ መስሪያ ጥሬ ዕቃ እና የቤት ክዳን ቆርቆሮ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ምርቶቹ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በማድረግ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ ማስቀረት መቻሉን አቶ ኢያሱ ስምዖን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የ1 ሺህ 467 ላኪዎችን ጥያቄ በመቀበል በ380 ሺህ 209 ሜትሪክ ቶን አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ የወጣላቸው ወጪ ምርቶች ላይ የኢንስፔክሽን ሥራ ለማከናወን ታቅዶ÷ በ163 ሺህ 752 ነጥብ 97 ሜትሪክ ቶን ላይ የኢንስፔክሽን ሥራ በማከናወን ፈቃድ ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡
ለአፈጻጸሙ ዝቅ ማለትም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ወደ ሱዳን የሚላኩ የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች የወጪ ምርቶች መጠን መቀነስ ማሳየታቸው በምክንያትነት ተነስቷል፡፡
እንዲሁም 779 ሜትሪክ ቶን÷ አኩሪ አተር፣ ቀይ ቦለቄ፣ ሰሊጥ፣ ባቄላ እና ዥንጉርጉር ቦለቄ ላይ በተደረገ የላቦራቶሪ ፍተሻ አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃን ባለማሟላታቸዉ እንደገና ተበጥረው ጥራታቸውን ጠብቀው ወደ ውጭ ሀገር እንዲላኩ መደረጉንም ነው የተናገሩት።
የግብርና የወጪ ምርቶች ከኢትዮጵያ ደረጃ መስፈርት በተጨማሪ በተቀባይ ሀገራቱ መስፈርት መሰረት ላኪዎች የሽያጭ ኮንትራት ስምምነት መስፈርትን አሟልተው እንዲልኩ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ሕጋዊ ሥነ ልክና ተስማሚነት ሥርዓትን ማጠናከርና ማዘመንን በተመለከተም÷ በ645 ሺህ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እና በገበያ ላይ ያሉ አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ የወጣላቸው የመለኪያ መሳሪያዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ታቅዶ በደንበኞች ጥያቄ መሰረት ለ922 ሺህ 536 የመለኪያ መሳሪያዎች የቬሪፊኬሽን አገልግሎት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
እነሱም÷ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ 141 ሺህ 935 የክብደት ማነጻጸሪዎችና ሚዛኖች፣ 741 ሺህ 657 የርዝመት መለኪያዎች፣ 125 ተሸጋጋሪ ሚዛኖች፣ 38 ሺህ 819 የፈሳሽ መለኪያ (የውኃ ቆጣሪና ፍሎው ሜትር) ናቸው፡፡
ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ እና በግብይቱ ውስጥ የሚገኙ 900 የጤናና የደኅንነት የመለኪያ መሳሪያዎች ላይ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ታቅዶ÷ 750 በጤና ተቋማት ላይ የሚገኙ የሙቀትና የግፊት መለኪያ መሳሪያች ላይ ኢንስፔክሽን በማድረግ ትክክለኛነት የማረጋገጥ ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!