Fana: At a Speed of Life!

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል ተልዕኮውን እንዲወጣ ከፋይናንስና ሰው ሃይል አንጻር አባል ሀገራት ዋጋ ከፍለዋል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል የሚጠበቅበትን ተልዕኮ እንዲወጣ ከፋይናንስ፣ ሰው ሃይልና ጊዜ አንጻር አባል ሀገራት አስፈላጊውን ዋጋ ከፍለዋል ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል የአባል ሀገራት ኢታማዦር ሹሞችና የፖሊሲ አውጭ አካላት ስብስባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር÷ በአፍሪካ በርካታ ችግሮች እያጋጠሙ መሆኑን በመጥቀስ፥ የአንድ ሀገር ችግር የጎረቤት ሀገራትም ችግር በመሆኑ በትብብር መስራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው ÷ ሽብርተንነት፣ ኢ-ሕገመንግስታዊ የሆነ የመንግስታት ለውጥና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች በአፍሪካ በተደጋጋሚ እየተከሰቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህ ስብሰባም እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ገቢራዊ ሃሳቦችን እንደሚያቀርብ ተስፋቸውን ገልፀዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ስብሰባው የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል ረቂቅ የድርጊት እቅድና በጀትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ዶክመንቶች ጋር ትኩረቱን አድርጎ እንደሚወያዩ ተናግረዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጌታቸው ሽፈራው÷ ባለፉት ቀናት የድርጅቱን ሁለንተናዊ ቁመናና ተቋማዊ ቅርፅ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሃሳቦች መቅረባቸውን አስረድተዋል።

ስብሰባው በኢታማዦር ሹሞች ደረጃ ለሁለት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን ለድርጅቱ የተልዕኮ አፈፃፀም አስቻይ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.