Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ስድስት ወራት 222 ቢሊየን ብር ጠቅላላ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት 222 ቢሊየን ብር ጠቅላላ ገቢ መገኘቱ ተገለፀ፡፡

በበጀት ዓመቱ 438 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት የታቀደ ሲሆን÷ ባለፉት ስድስት ወራት 222 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል፡፡

ያለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጠቅላላ ገቢ 172 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እንደነበር በፕላን እና ልማት ሚኒስቴር በቀረበው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የስድስት ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ተመላክቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የመንግስት ጠቅላላ ወጪ 293 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ሲሆን÷ ያለፈው ዓመት የመንግስት ጠቅላላ ወጪ 235 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡

እንዲሁም የወጪ ዕድገት ካለፈው ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ሲሆን፥ በሥድሥት ወራቱ ውስጥ 68 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ከጠቅላላ ወጪ 49 በመቶውን ሸፍኗል።

የ2015 ዓ.ም በመጀመሪያው ስድስት ወራት ከውጭ ቀጥታ የበጀት ድጋፍ 20 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ይገኛል ተብሎ የታቀደ ሲሆን÷ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ገቢ መሆኑም ነው የተመላከተው።

እንዲሁም የታክስ ገቢ ካለፈው ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር በ30 ነጥብ 4 በመቶ ሲጨምር ታክስ ያልሆኑ ገቢዎች ደግም የ7 ነጥብ 3 በመቶ እድገት አሳይቷል ተብሏል።

በማምረቻ ዘርፍ 308 ነጥብ 89 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 227 ነጥብ 61 ሚሊየን ዶላር የተገኘ ሲሆን፥ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10 ነጥብ 65 ሚሊየን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል ነው የተባለው።

ከማዕድን ምርቶችን ጋር በተያያዘም 324 ነጥብ 67 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 116 ነጥብ 54 ሚሊየን ዶላር ሲገኝ፥ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 281 ነጥብ 52 ሚሊየን ዶላር ጋር ሲነፃፀር 164 ነጥብ 97 ሚሊየን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል።

በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት 2 ነጥብ 95 ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዶ 1 ነጥብ 893 ቢሊየን ዶላር መሳብ የተቻለ ሲሆን ÷አፈጻጸሙ 64 በመቶ ሲሆን ይህም ከባለፈው ዓመትተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 16 ነጥብ 3 በመቶ እድገት እንዳለው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በአጠቃላይ 171 ፕሮጀክቶችን (77 ወደ ትግበራ እና 94 ወደ ማምረት/አገልግሎት መስጠት) ለማሻገር ታቅዶ 149 ፕሮጀክቶች (73 ወደ ትግበራ እና 76 ወደ ማምረት/አገልግሎት መስጠት) የተሸጋገሩ ሲሆን አፈጻጸሙም 87 በመቶ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በ”የቴሌብር” አገልግሎት 27 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን በማፍራትና በስድስት ወራት ውስጥ አጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ 166 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር የግብይት መጠን በማንቀሳቀስ የ82 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ገቢ ማስገኘት ተችሏል፡፡

በአጠቃላይም አገልግሎት ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ድረስ 263 ቢሊየን ብር ግብይት ተካሂዷል ነው የተባለው፡፡

በ2015 ዓ.ም በግብርና ዘርፍ ዕድገት ትንበያ 6 ነጥብ 3 በመቶ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድገት ትንበያ 8 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፍ ዕድገት ትንበያ 7 ነጥብ 5 በመቶ መሆኑም በሪፖርቱ ተካቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.