የአፍሪካ ህብረት አመታዊ ጉባኤ ነገ በስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ይጀመራል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 36ኛው የአፍሪካ ህብረት አመታዊ ጉባኤ ነገ በስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ እንደሚጀምር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ በስብሰባው ኢትዮጵያ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በተመራ ልዑክ ትሳተፋለች ብለዋል።
በዚሁ ስብሰባ ከ51 ሀገራት የተውጣጡ የልዑካን ቡድኖች ይሳተፋሉ ተብሏል።
ነገ ከሚጀምረው 42ኛው የስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ አስቀድሞ በቋሚ መልእክተኞች ደረጃ ውይይቶች መጀመራቸውን አምባሳደር መለስ አለም አንስተዋል።
ከአፍሪካ ውጭ ያሉ ሀገራትም ለጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ የሚሳተፉበት ጉባኤ መሆኑን ያነሱት አምባሳደር መለስ ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ጠንካራ ስራ የሚሰራበት እንደሆነ ገልፀዋል።
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያም መልካም ተሞክሮ የምታጋራባቸውን ስኬቶች የምታጎላበት ፤በብርቱ ፈተና ውስጥ በነበረችበትም ወቅት ከጎኗ ለቆሙ አፍሪካውያን ወንድሞች አፍሪካዊ መፍትሄ ለማምጣት ለተደረገው ጥረት እውቅና የምትሰጥበት ይሆናል ብለዋል።
ጉባኤው የአዲስ አበባን የአፍሪካን የዲፕሎማሲ የሚያፀና እንደመሆኑ ኢትዮጵያ ልትጠቀምበት ተዘጋጅታለችም ነው ያሉት፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የጎንዮሽ ስብሰባዎችና ውይይቶችን ታደርጋለች፤ ግንኙነቶችንም ለማጠናከር ትጠቀምበታለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሀብታሙ ተ/ስላሴ