Fana: At a Speed of Life!

በጦርነት ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነት ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ሪፖርቱን አቅርቧል፡፡

በሪፖርቱ እንደተገለጸው በጦርነት ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት “አዲስ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤት” የሚል የትምህርት ቤት ዲዛይን ተዘጋጅቶ እየተሰራ ሲሆን፥ ከወደሙት 1 ሺህ 335 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሃምሳዎችን ስራ ለማስጀመር እየተሰራ ነው ብሏል፡፡

በሰዎች ለሰዎች ድርጅትና በዳያስፖራ ማህበረሰብ ድጋፍ 21 ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ስምምነትና የቦታ ርክክብ መፈጸሙንም ጠቅሷል።

31 ሺህ 908 የጐልማሶች መሠረታዊ ትምህርትና የሙያ ክህሎት ስልጠና የሚሰጡ ጣቢያዎች መከፈታቸውም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በመመዘኛው መሰረት የተቋቋሙ የማህበረሰብ መማማሪያ ማዕከላት 102 መድረሳቸውም ተጠቁሟል፡፡

12ኛ ክፍል የፈተና አሰጣጥ ስርዓትን ከኩረጃ የጸዳ ማድረግን በተመለከተም ውጤታማ ስራ መሰራቱ ተነስቷል፡፡

በዚህም የመፈተኛ ጣቢያ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን በማድረግ፣ ፈታኝ መምህራንን ከክልል በመቀያየር እና ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲ በማጓጓዝ ፈተናው ለ954 ሺህ 560 ተማሪዎች በተሳካ መልኩ እንዲሰጥ መደረጉን በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.