Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል በምርምር የእንስሳትን ዝርያ በማሻሻል አርሶ-አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በልየታ ምርታማ የሆኑ እንስሳትን በመምረጥ እና ዘረ-መላቸውን በምርምር በማሻሻል አርሶ-አደሩን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ተገለጸ፡፡

በደቡብ ክልል ግብርና እና ምርምር ኢኒስቲትዩት የሐዋሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ተመራማሪ ዶክተር አመልማል ዓለማየሁ ÷ በተጨማሪም በጌዴኦ እና ሐላባ ዞኖች እንዲሁም በሲዳማ ክልል ማዕከሉ በርካታ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የበግ እና የፍየል የሥጋ ምርት ፣ የላም ወተት ምርት እና ጥራት ፣ የእንቁላል እና የሥጋ ዶሮዎች ምርት እና ጥራት በምርምር ማሻሻል ላይ በስፋት እንደሚሠራም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል፡፡

ሀገር በቀል ዝርያ ያላቸውን ምርታማ የሥጋ እንስሳትን ከአርሶ አደሩ ጋር በመሆን በመለየት በቀጣይ ምርምር ዘረ-መላቸውን የማሻሻል እና ምርታቸውን ከፍ የማድረግ ሥራ እደሚሰራ ጠቅሰዋል፡፡

እንስሳትን በመረጣ የማሻሻል ሂደት በእንስሳቱ የምርታማነት እና ዕድገት ባህሪያት ላይ መሻሻል መኖሩን በሳይንሳዊ መንገድ መረጋገጡን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ከአርሶአደሩ ጋር በመተባበር ከመረጧቸው የበግ ዝርያዎች መካከል በሲዳማ ክልል የሚገኘው የአበራ በግ በሥጋ ምርታማነቱ ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በሥጋ ምርታቸው እና በፈጣን ዕድገታቸው ግንባር ቀደም የሆኑት የቦንጋ እና የዶዮገና በግ ዝርያዎች በማኅበረሰብ አቀፍ ዝርያ ማሻሻል የተገኙ ስለመሆናቸውም ነው የሚናገሩት።

የቦረና ዝርያ ከሲዳማ ጋር በማዳቀል አመርቂ የሥጋ እና የወተት ምርት ያላቸውን የቁም እንስሳት እና የወተት ላሞች ለአርሶአደሩ ማበርከት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

የመንግስት ትኩረት የእርሻውን ዘርፍ ከማዘመን በተጨማሪ የሥጋ እና የወተት እንስሳትን ምርት እና ጥራት ማሻሻል ላይ ጭምር መሆኑንም ገልጸዋል።

በዓለማየሁ ገረመው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.