በኬንያ ያጋጠመውን ድርቅ ተከትሎ ብሔራዊ የፀሎት ቀን ታወጀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በኬንያ ለ 6 ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ባለመዝነቡ ያጋጠመውን ከፍተኛ ድርቅ ተከትሎ በዛሬው ዕለት ብሔራዊ የፀሎት ቀን ታወጀ፡፡
አዋጁን ያስነገሩት የሀገሪቷ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ናቸው ተብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ሩቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ዕለተ-ዕሁድ ከኬንያ መዲና ናይሮቢ በ160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውና ድርቅ አብዝቶ ባጠቃት ናኩሩ ከተማ ተገኝተው ሕዝቡ አብዝቶ እንዲፀልይ ማሳሰባቸውን አፍሪካ ኒውስ አስታውሷል፡፡
የኬንያውን ፕሬዚዳንት ተከትሎ የሀገሪቷ የሃይማኖት አባቶች በኅብረት በመሆን ፈጣሪ ድርቁን እንዲያቀልላቸው ሕዝቡ ወደ ፈጣሪው እንዲፀልይ ሀገራዊ ጥሪ አቅርበዋልም ነው የተባለው፡፡
ቀደም ሲል ፕሬዚዳንት ሩቶ ለሕዝቡ የገቡት ተስፋ እና ስትራቴጂያዊ የኢኮኖሚ መነቃቃት ያለ ዝናብ ዕውን ሊሆን የማይችል ኅልም ብቻ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
ዊሊያም ሩቶ ÷ “እንደ መንግስት የምግብ ደኅንነታችንን ለማረጋገጥ ዝርዝር ዕቅድ አውጥተን ፣ ዘር እና በርካታ የአፈር ማዳበሪያ አዘጋጅተን ፣ ግድብ መሥራትን ጨምሮ ውሃ የምናቁርበትን ስትራቴጂ ዘይደን ነበር” ብለዋል፡፡
አክለውም “አሁን የምንጠብቀው ፈጣሪ ዝናብ እንዲልክልን ነው” ብለዋል፡፡ ሁሉም እንደ ዕምነቱ ለሀገሩ እንዲፀልይም ነው የጠየቁት፡፡