የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ በሐዋሳ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባዔ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡
ምክር ቤቱ በጉባዔው የበጀት ዓመቱ የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት እንደሚያደርግ ተጠቁሟል፡፡
በጉባዔው ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፋጤ ሰርሞሎ ÷ ለህዝብ ቅሬታ ምንጭ የሆኑ ምክንያቶች እንዳያንሰራሩ አድርጎ መፍታት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በትምህርት ዘርፍ የታየውን ክፍተት የመለየቱና የማረሙ ተግባርም በየደረጃው ባሉ እርከኖች ሊታይና ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል ብለዋል፡፡
በግብርው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት የተገኘባቸው እንደሆኑ አንስተዋል፡፡
የመዳኒት አቅርቦት ላይ ፣ የሴቶች ተጠቃሚነትን በተመለከተ እንዲሁም በሌማት ትሩፋት ሥራዎችና መሰል መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አፈ ጉባዔዋ አፅንኦት ሰጥተዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ በበኩላቸው ÷ የህዝቡን የአደረጃጀት ጥያቄዎች ለመመለስ የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ስኬታማና ያለ ምንም ችግር የተካሄደ ነበር ብለዋል።
የክልሉ መንግስት የህዝበ ውሳኔውን ውጤት ወደ ተግባር በመለወጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈንና የህዝቡን ፍላጎትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል ።
ለህዝቦች ወንድማማችነት፣አንድነትና የጋራ ባሕላዊ ዕሴቶች መጠናከር ጠንክረን እንሠራለን ያሉ ሲሆን ህዝበ ውሳኔው ስኬታማ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ላደረጉ አካላትም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የ6 ወራት አፈጻጸም ላይ እየተወያየ ነው።
የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ሹመት ለምክር ቤቱ ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፡፡
በብርሃኑ በጋሻው