42ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ ተጀመረ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 8 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 42ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬ አዲስ አበባ ተጀምሯል።
በምክር ቤቱ ስብስባ ላይ የሕብረቱ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ተወካዮች ይሳተፋሉ።
በስብስባው ላይ ለመሳተፍ ከተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል የሶማሊያ፣ ናይጄሪያ፣ ኮሞሮስ፣ ታንዛንያ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሴራሊዮን፣ ኮትዲቭዋር፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዚምባቡዌ እና ማሊ ይገኙበታል።
የምክር ቤቱ ስብሰባ የአፍሪካ ሕብረት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ በጥር ወር 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባደረገው 45ኛ መደበኛ ስብስባ የተወያየባቸው አጀንዳዎች እንደሚቀርቡበት ሕብረቱ አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ለሁለት ቀናት በሚያደርገው ስብሰባ በኮሚቴው የቀረቡለትን የተለያዩ አጀንዳዎች ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ምክር ቤቱ “የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራን ማፋጠን” የአፍሪካ ሕብረት እ.አ.አ የ2023 መሪ ሃሳብ ሆኖ እንዲሰየም በቀረበው የመነሻ ሃሳብ ላይ እንደሚወያይ የአፍሪካ ሕብረት አስታውቋል።
የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ በውይይቱ ያጸደቃቸውን አጀንዳዎች ለ36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ያቀርባል።
የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 11 እና 12 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ ኢዜአ ዘግቧል።