Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል-ግብረ ሃይሉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል አስታወቀ፡፡

የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይሉ የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እንዲጠናቀቅ  አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ስምሪት በመውሰድ ወደ ስራ መግባቱ ተገልጿል፡፡

በጉባኤው ለመሳተፍ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ መሪዎችን እና ዲፕሎማቶችን ደህንነት ማረጋገጥ የፀጥታ አካላት ሃላፊነት መሆኑን የገለፀው ግብረ ሃይሉ÷ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል፡፡

በሆቴሎች፣ በመዝናኛ እና በገበያ ስፍራዎች እንዲሁም እንግዶቹ ከቦታ ቦታ በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ላይ  ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡

ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍና ትብብር ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አንስቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ እና ምንም አይነት የደህንነት ስጋት እንዳይኖር ከፀጥታ አካላቱ ጋር ተቀናጅተው በመስራት እንደወትሮው ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉ ተጠይቋል፡፡

በተለይም መንገዶች ዝግ በሚደረጉበት ወቅት አሽከርካሪዎች እና እግረኞች በትዕግስት በመጠበቅ ወይም ሌሎች አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም ለሀገር ገፅታ ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙና የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘት በስልክ ቁጥር 011-111-01-11፣ 011-552-63-03፣ 011-552-40-77፣ 011-554-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ መስጠት የሚቻል መሆኑን ግብረ ሃይሉ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.