Fana: At a Speed of Life!

ከ16 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት ከ16 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው መኃኒቶች፣ የህክምና መሳሪያዎች እና የመዋቢያ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

ባለስልጣኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቀው÷ ከ10 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች እና መድኃኒት ለማምረት የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል።

በተጨማሪም ከ 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የህክምና መሳሪያዎች ላይ የጥራት ቁጥጥር በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ጥቅም ላይ ውለዋል ነው ያለው።

ከዚህ ባለፈም ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የመዋቢያ ምርቶችና የመዋቢያ ምርቶችን ለማምረት የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል ተብሏል፡፡

በተጠናቀቀው ሥድስት ወር ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ቶን ምግብ፣ የምግብ ጥሬ ዕቃ እና የሕጻናት ወተት ደኅንነቱ ተረጋግጦ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱም ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ 53 የምግብ ፋብሪካዎች እና 439 የምግብ ላኪ፣ አስመጪና አከፋፋይ ድርጅቶች የብቃት ማረጋገጫ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን ነው ያስታወቀው።

በ355 የምግብ ፋብሪካዎች እና በ280 የምግብ ላኪ፣ አስመጪና አከፋፋይ ድርጅቶች ላይ የስጋት ተኮር ፍተሻ ተከናውኖ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት እየሠሩ መሆኑን ባለስልጣኑ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በግማሽ ዓመቱ 449 መድኃኒቶችና 518 የህክምና መሳሪዎች ተመዝግበው የገበያ ፈቃድ ያገኙ ሲሆን÷ በአጠቃላይ እስካሁን ባለስልጣኑ 5 ሺህ 799 መድኃኒቶችን በመመዝገብ እንዲሁም ለ60 ሺህ 406 የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች የገበያ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡

በጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ ለሚያመርቱ 16 ድርጅቶች እና 240 የመድኃኒት አስመጪና አከፋፋዮች አዲስ የብቃት ማረጋገጫ መስጠቱንም ነው የገለጸው።

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.