ኢትዮጵያና ናሚቢያ በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ናሚቢያ በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ እና የናሚቢያ ምክትል ጠቅላይ ማኒስትርና የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ኔቱምቦ ናንዲ ንዳይትዋህ ተፈራርመዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት ÷ ሁለቱ ሀገራት የቆየ የዴሞክራሲ ትስስር አላቸው።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የመከላከያና የጸጥታ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ስምምነት ተፈራርመናል ነው ያሉት።
ወታደራዊ ስልጠና በአየር ሃይል፣ ባህር ሀይልና ሌሎችም ዘርፎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለማከናወን የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ገልጸዋል።
ኔቱምቦ ናንዲ ንዳይትዋህ በበኩላቸው÷ የሁለቱ ሀገራት ትብብር ከናሚቢያ ቅኝ ግዛት ነጻ መውጣት ጋር በጥበቅ የተቆራኘ ብለዋል።
ናሚቢያ ከቅኝ ገዥዎች ነፃ በመወጣችበት ወቅት የኢትዮጵያ ተሳትፎ የጎላ እንደነበርም አንስተዋል።
ሀገራቱ በዘርፉ በስልጠና፣ በአየር መንገድ፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲሁም በባህል መስኮች በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ነው የገለጹት።
ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና በናሚቢያ መካከል ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር መሰረት የሚጥል መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው በመሆኑ በቀጣናው ስራዎች ላይ ውጤታማ ዘመቻ ማከናወን ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።