Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ ሙፈሪሃት ከአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሶሎሞን ኳይኖር ጋር ተወያዩ፡፡

ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ተገቢውን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ ማስቻል የሀገርን ራዕይ እውን ለማድረግ የሚያስችል ቀዳሚ እርምጃ መሆኑ በውይይቱ ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ላይ ሚኒስትሯ÷ በክህሎት የበቁና በሥራ ፈጠራ እሳቤ የተቃኙ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችሉ የተለያዩ እቅዶች እየተተገበሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በተለያዩ ዘርፎች ላይ በአጋርነት ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት  ሶሎሞን ኳይኖር በበኩላቸው÷ የአፍሪካ ልማት ባንክ የፋይናንስ አካቶ ትግበራን፣ የኢንተርፕርነርሺፕና የቢዝነስ ሥነ-ምህዳር ልማትንና የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍን በሚመለከቱ ሦስት ምሰሶዎች ላይ አተኩሮ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ በሚገኘው ፕሮግራም ወጣቶችን በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የፋይናንስ ድጋፍ ሥርዓት በመዘርጋት ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

የፋይናንስ ድጋፉ በዝቅተኛ ወለድ ወይም ያለወለድ የሚሰጥ ፍትሃዊ የብድር ሥርዓትን ያካተተ በመሆኑ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ያለባቸውን የፋይናንስ እጥረት በመፍታት የሥራ ዕድልን በመፍጠር በኩል ጉልህ ሚና እንደሚጫወት መገለጹን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.