አቶ ደመቀ መኮንን ከተለያዩ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ውጤታማ ውይይት አካሄዱ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተለያዩ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ሁለተኛ ቀን ውሎን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም÷ለጉባዔው በርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ አምባሳደሮች እንዲሁም የሌሎች ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል ብለዋል።
“ዓለም አዲስ አበባ ላይ ተሰብስቧል ቢባል ማጋነን አይሆንም” ያሉት ቃል አቀባዩ÷በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ መዲና እንዲሁም የአፍሪካውያን የዲፕሎማሲ መዲና መሆኗን ያረጋገጠችበት ነው ብለዋል፡፡
ከትናንት የቀጠለው የአፍሪካ ህብረት የአስፈጻሚዎች ስብሰባ ዛሬም በተለያዩ ሁነቶች መቀጠሉን ጠቅሰዋል።
ዛሬ አቶ ደመቀ መኮንን ከጋቦን፣ ጋምቢያ፣ ማላዊ፣ ከኖርዌይ፣ ከፖርቹጋል፣ ሊቢያና ቱኒዚያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያይተዋልም ነው ያሉት፡፡
ውይይቱ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታና የሁለትዮሽ ግንኙነትን የሚመለከት ሲሆን÷ አቶ ደመቀ ለሀገራቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አሁናዊ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አብራርተዋል ነው ያሉት።
ሀገሪቱ ለሰላም የምትሰጠው ቦታ ትልቅ መሆኑንና መንግስት ለዚህ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ማድረጋቸው በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹም ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚሆኑ ገልጸው÷የኢትዮጵያ ችግር የሌሎችም ችግር፣ የኢትዮጵያ እድገት የሌሎችም እድገት መሆኑን አንስተዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያን መጠናከር እንደሚፈልጉም ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውን አምባሳደር መለስ ዓለም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን÷ በቀጣይ በመሪዎች ደረጃ ስብሰባው ይቀጥላል ነው የተባለው።
በታሪኩ ለገሰ