የሀገር ውስጥ ዜና

የዓድዋ ድልን ታላቅነት በሚመጥን መልኩ ለማክበር ዝግጅት መጀመሩን የተቋቋመው ኮሚቴ ገለጸ

By Shambel Mihret

February 16, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድልን በዓል የድሉን ታላቅነት በሚመጥን መልኩ ለማክበር ዝግጅት መጀመሩን የተቋቋመው ኮሚቴ አስታውቋል፡፡

ኮሚቴው ከመከላከያ ሚኒስቴር፣ ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ለበዓሉ በድምቀት መከበር አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ተብለው እምነት ከተጣለባቸው አካላት  የተቋቋመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ÷ የአድዋ ድል በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በጣሊያን ቅኝ ገዥዎች እና ለነፃነት በታገሉት የኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል በአድዋ ተራራ እና አካባቢው በተደረገ ጦርነት ኢትዮጵያውያን ጠላትን ድባቅ በመምታት አንፀባራቂ ድል የተጎናፀፋበት በዓል ነው ብለዋል።

የአፍሪካውያንን የትግል ታሪክ የቀየረ ታላቅ በዓል መሆኑን በመጥቀስም፥ ድሉ በቀላሉ የተገኘ ሳይሆን በርካታ የኢትዮጵያ ጀግኖች የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው ለእኛ ለልጆቻቸው የሰጡን ዘመን ተሻጋሪ ታሪካችን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በበኩላቸው÷ የአድዋ ድል እንደማንኛውም የአውደ ውጊያ ድሎች በውጊያ የተገኘ ብቻ ሳይሆን ዘመንም ወንዝም ተሻጋሪ ታሪክ ብለዋል፡፡

መገፋትን የሚጠሉ እና ነፃነትን አብዝተው የሚሹ አባቶች የአካል እና የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው ለልጆቻቸው በክብር ያስረኩቡት ታላቅ ታሪክ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በበአሉ ዕለት 21 ጊዜ መድፍ እንደሚተኮስ፣ ጀግና አርበኞችን ለማስታወስ ከጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር ጋር በጋራ በመሆን በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ አደባባይ የአበባ ጉንጉን እንደሚቀመጥ ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡