የሀገር ውስጥ ዜና

በመተከል ዞን የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ባህላዊ የእርቅ ስነ ስርዓት ተካሄደ

By Meseret Awoke

February 16, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል የሰላም ጥሪ ተቀብለው ከገቡ የጉህዴን ታጣቂዎች ጋር ባህላዊ የእርቅ ስነ ስርዓት በወምበራ ወረዳ ተካሂዷል።

የተገኘውን ሰላም በመጠቀም ወደ ልማት ለመግባት በወምበራ ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ታጣቂዎችና የመንግስትን የሰላም ጥሪ ከተቀበሉ ወገኖች ጋር በአባቶች አማካኝነት ባህላዊ የእርቅ ስነ ስርዓት ተደርጓል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አቢዮት አልቦሮ እንዳሉት ፥ ባለፉት ዓመታት የነበረውን ግጭት በይቅርታና ምህረት የቆየውን አብሮነትና አንድነት በማስቀጠል የልማትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን ይገባል።

ጥላቻና በቀልን በሰላም መጋረጃ በመዝጋት መጪውን ጊዜ በነበረን የጋራ በሆኑ መልካም እሴቶችን ማዳበር መሆኑን በመረዳት በአካባቢው ያለውን ጸጋ በጋራ በማልማት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል ኃላፊው።

የህዝቡን ማህበራዊ እረፍት የማይፈልጉ ሃይሎች እኩይ አጀንዳን ማስወገድ ከተቻለ በየደረጃው የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መንግስት እንደሚፈታ ተገልጿል።

ወጣቱ ትውልድ የአካባቢውን ጸጋ ተጠቅሞ ሁሉን አቀፍ ልማቶች ላይ ተሳታፊ መሆን እየተቻለ የግለሰቦችና የጠላት አጀንዳን ተሸክሞ ያለአግባብ መስዋዕትነት መክፈል መብቃት እንዳለበትም ነው በውይይቱ የተነሳው።

የሰላምን ጥሪ የተቀበሉ ወጣቶች ፍላጎትንና የትምህርት ደረጃን መሰረት ባደረጉ መልኩ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የክልሉ መንግስት ምቹ ሁኔታዎች እየፈጠረ መሆኑንም አቶ አቢዮት አብራርተዋል።

የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች በበኩላቸው ፥ ከወሬና የሀሰት ትርክት በመራቅ ዘላቂ ሰላምን በማስቀጠል ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ መናገራቸውን ከዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።