ከሕገ ወጥ መድኃኒት፣ ምግብና እና ህክምና መሳሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በ71 መዝገቦች ላይ ውሳኔ ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቁጥጥር ከሚደረግባቸው የምግብ፣ መድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያ፣ አልኮል፣ ትንባሆ እና የውበት መጠበቂያ ምርቶች ጋር በተያያዘ ከ200 በላይ መዝገቦች የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ ነው፡፡
የምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ 1112/2011 ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በ71 መዝገቦች ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል ሲል የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በዚህም የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ ቅጣትን ጨምሮ ከ2 እስከ 10 ዓመት ጽኑ እስራት መወሰኑ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም 55 መዝገቦች በክርክር ሂደት እንዲሁም 78 መዝገቦች ደግሞ በምርመራ ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ከምግብ ጋር በተገናኘ የወንጀል ዓይነቶቹ÷ የምግብ ቅቤ፣ ዘይት፣ ማር፣ በርበሬን ከባዕድ ነገር መቀላቀል÷ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈ ምግብ ለህብረተሰቡ ማቅረብ፣ በአዮዲን ያልበለፀገ የምግብ ጨው ለሽያጭ ማቅረብ፣ የብቃት ማረጋገጫ ሳይኖር ምግብ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትና ማከፋፈል መሆናቸውን ባለስልጣኑ አስረድቷል፡፡
እንዲሁም ሕገ ወጥ መድኃኒት ማዘዋወር፣ ያልተመዘገበና የብቃት ማረጋገጫ የሌለው መድኃኒት ለህብረተሰቡ ማቅረብ፣ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈ መድኃኒት ለሽያጭ ማቅረብ፣ ከደረጃ በታች የሆነ መድኃኒትና የህክምና መሳሪያ መሸጥ የሚሉት ከመድኃኒቶች እና የህክምና መሳሪያዎች ጋር የተገናኙ የወንጀል ዓይነቶች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
ከውበት መጠበቂያ ምርቶች እና ትምባሆ ጋር በተገናኘ የውበት መጠበቂያ ምርት ያለፈቃድ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ ማከፋፈል እና መሸጥ፣ ሕገ ወጥ የትንባሆ እና የውበት መጠበቂያ ምርት ለህብረተሰቡ ማቅረብ እና የሺሻ ምርቶችን ለህብረተሰቡ ማቅረብ መሆናቸውን ነው ባለስልጣኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጸው፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!