ኢትዮጵያ በትምህርት ላይ በተጠራው ዓለምአቀፍ የሐብት ማሰባሰቢያ መድረክ ተሳተፈች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ በትምህርት ላይ በተጠራው ዓለምአቀፍ የሐብት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ሚኒስትሩ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የ222 ሚሊየን ሕጻናት ህልም ዕውን እንዲሆን እናግዝ ሲሉ ጥሪ አቀርበዋል።
“በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ትምህርትን መምራት” በሚል መሪ ሐሳብ በተካሔደው መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አካፍለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ፣ ድርቅ ፣ ግጭትና ሌሎች ተደራራቢ ጫናዎችን ተቋቁማ ትምህርትን በማስቀጠል በ10 ሚሊየን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርት ላይ እንዲቆዩ ማድረግ እንደቻለች አንስተዋል፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ለትምህርቱ ዘርፍ 22 ከመቶ በላይ በጀት መድቧልም ብለዋል፡፡
በመድረኩ በቀረበው ጥናታዊ ሪፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ 78 ሚሊየን ሕጻናት ወደ ትምህርት ሄደው እንደማያውቁ እና መድረኩ መፍትሔ ለመፈለግ ወሳኝ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።