ተመድ በቱርክ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች 1 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ጠየቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቱርክ የመሬት መንቀጥቀጥ ጉዳት የደረሰባቸውን ከ5 ሚሊየን በላይ ዜጎች ለመርዳት 1 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ጠይቋል፡፡
በደቡባዊ ቱርክ እና ሰሜናዊ ሶሪያ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ36 ሺህ በላይ ቱርካውያንን እንዲሁም በሶሪያ ደግሞ እስካሁን 5 ሺህ 800 ዜጎች ለህልፈት መዳረጉን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ባለፈው ሳምንት ቱርክን የጎበኙት የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች እና አስቸኳይ ዕርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትዝ÷ ቱርካውያን በቃላት ሊገለፅ የማይችል የከፋ ጉዳት አጋጥሟቸዋል ብለዋል፡፡
በዚህ አስከፊ ጊዜ ከቱርካውያን ጎን በመቆም የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ አለብን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በቱርክ እስከ ባለፈው ረቡዕ ድረስ በርካታ ሰዎች ከህንፃ ፍርስራሽ ውስጥ በህይወት ቢገኙም አሁን ላይ ከአደጋው በህይወት ተርፈው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱ ነው የተነገረው።
የቱርክም ይሁን የሶሪያ ባለስልጣናትም ምን ያክል ሰዎች እንደጠፉ ያሉት ነገር የለም ነው የተባለው።
ቱርካውያን የመሬት መንቀጥቀጡን የሚቋቋሙ ደረጃቸውን የጠበቁ ህንፃዎችን ባለመግንባታቸው ለደረሰው ጉዳት የቱርክን የከተማ ልማት እየወቀሱ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡
የቱርክ መንግስት ለህንፃዎች መፍረስ ተጠያቂ ናቸው በሚል በጠረጠራቸው ግለሰቦች ላይ ማጣራት ለማድረግ ቃል የገባ ሲሆን እስካሁንም ከ100 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ትዕዛዝ መስጠቱን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡