የጊኒ ቢሳው ፕሬዚዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎበኙ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጊኒ ቢሳው ፕሬዚዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎበኙ።
በኢንስቲትዩቱ በነበራቸው ጉብኝት ስለኢንስቲትዩቱ እና ኢትዮጵያ በዘርፉ እያደረገች ስላለው እንቅስቃሴ በኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት ስለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል በማመስገን፥ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ በተለይም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እየሠራች ያለችው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገሪቷ ቴክኖሎጂው በግብርና፣ በጤና፣ በገንዘብ ነክ ጉዳዮች እና ሌሎችም ዘርፎች ያለውን አበርክቶ በጊዜ በመረዳት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሯ እጅግ የሚበረታታ መሆኑን ጨምረው መግለጻቸውን ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
አፍሪካም እንደ አህጉር ለጀመረችው የቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዞ የኢትዮጵያ ጅማሮ በተምሣሌትነት ሊወሰድ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ አመላክተዋል።