የጊኒ ቢሳው ፕሬዚዳንትና የልዑካን ቡድናቸው የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጊኒ ቢሳው ፕሬዚዳንት ኡማሮ ሲስኮ ኢምባሎ እና የልዑክ ቡድናቸው የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን ጎበኙ፡፡
ፕሬዚዳንቱ እና ልዑካቸው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎትን የሪፎርም እና የተልዕኮ ሥራዎች የሚያስቃኘውን ዲጂታል ኤግዚብሽንና የመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤትን ጎብኝተዋል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ሲሳይ ቶላ ÷ ኢትዮጵያ እና ጊኒ ቢሳው በተለያዩ መስኮች ስኬታማ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ከጊኒ ቢሳው አቻው ጋር በአቅም ግንባታ እና በመረጃ ልውውጥ መስኮች በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳለውም አመልክተዋል።
ይህም ሽብርተኝነት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች፣ የገንዘብና የመሣሪያ ዝውውርን በመግታት ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ሰላም እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
የጊኒ ቢሳው ፕሬዚዳንት ኡማሮ ሲስኮ ኢምባሎ በበኩላቸው÷በብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ሪፎርም ከተከናወነ በኋላ ባሉት ጥቂት አመታት የተመዘገበው ስኬት እና እንደ ሀገር የታዩትም ለውጦች እንዳስደመማቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በመረጃና ደኅንነት ዘርፍ የዳበረ ልምድ እንዳላት መገንዘባቸውን በመግለጽ የሁለቱ ሀገራት የመረጃና ደኅንነት ተቋማትም በጋራ ጉዳዮች በትብብር እንዲሠሩ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ፕሬዚዳንቱ አዲሱን የመከላከያ መሥሪያ ቤት የጎበኙ ሲሆን÷ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ሠራዊት ለመግንባት እያደረገች ያለችውን ጥረት አድንቀዋል።
ፕሬዚዳንት ኡማሮ ሱሳኮ ከኢትዮጵያ ለሀገራቸው መከላከያ የተለያዩ ልምድና ተሞክሮ መውሰዳቸውንም ገልፀዋል።
ጊኒ ከኢትዮጵያ ጋር ለዘመናት የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላት መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ በቀጣይ በተለያዩ መስኮች ወዳጅነትን በማጠናከር እንሠራለን ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገነኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብረሃም÷ ሁለቱ ሀገራት በቀጣይ በወታደራዊና ፀጥታ ጉዳይ በትብብር እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።