በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ የግሉ ዘርፍ በንቃት እንዲሳተፍ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ የግሉ ዘርፍ በንቃት እንዲሳተፍ ተጠየቀ።
ከ36ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ጎን ለጎን በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ የግሉ ዘርፍ የሚኖረው አስተዋጽኦ ላይ ያተኮረ ውይይተ ተካሂዷል።
በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምክትል ጸሃፊ ሃናን ሙርሲ÷ ዓለም አሁን የአቅርቦት ችግር በገጠማት ወቅት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና መምጣት እጅግ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ይህም ቀጣናዊ የአቅርቦት ትስስርን ለማሳደግና በአውሮፓ ህብረት ያሉ ዕድሎችን ለመጠቀም ለግሉ ዘርፍ ትልቅ እድል ይዞ የመጣ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ነጻ የንግድ ቀጣናውን ለማሳለጥ የሎጅስቲክና መሰረተ ልማት ላይ መዋለ ነዋይ ማፍሰስ እንደሚገባም አክለው መናገራቸውን ኢዜአ ዘገባ ዘግቧል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ነጻ የንግድ ቀጣናውን ተግባራዊ በማድረግ በኩል ስልጠናዎችን በመስጠትና ሌሎች ድጋፎችን እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ቢዝነስ ካውንስል ፕሬዚዳንት ዶክተር አማንይ አስፎር በበኩላቸው÷ አፍሪካ ያላትን ሃብት በመጠቀም ለማደግ የግሉ ዘርፍ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ መሰራት ይገባዋል ብለዋል።
በአፍሪካ ህብረት የምጣኔ ሃብት እድገት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና ማዕድን ኮሚሽነር አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ ለስራ እድል ፈጠራና ምጣኔ ሃብት እድገት ከፍተኛ እድል ይዞ የመጣውን የአፍሪካ ንግድ ቀጣና ባለሃብቶች እንዲጠቀሙበት መክረዋል።