Fana: At a Speed of Life!

አደጋን በመቆጣጠር ረገድ ተደራሽ ለመሆን እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አደጋ የመካለከልና የመቆጣጠር አቅምን ለማሳደግ የሪፎርም ሥራ መጀመሩን የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

አደጋን አስቀድሞ በመከላከል የህብረተሰቡ ግንዛቤ እና ጥንቃቄ እንዲጎለብት በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አደጋ ከደረሰ በኋላ በፍጥነት መድረስ ቢጠበቅም የመንገድ መዘጋጋት ስለሚፈጠር እንደሚፈተኑ በኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ቅርንጫፍ ጣቢያዎችን ማስፋፋት አንዱ መፍትሔ መሆኑ ታምኖበት 10ኛው ቅርንጫፍ ጣቢያ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ እየተገነባ ነው ብለዋል፡፡

በየካ እና ልደታ ክፍለ ከተሞችም ተጨማሪ  ቅርንጫፎችን ለመክፈት በሂደት ላይ ስለመሆኑም ነው የጠቆሙት፡፡

እንዲሁም ለአደጋ ተጋላጭ ተብለው በተለዩ አካባቢዎች ንዑስ ጣቢያዎችን በመክፈት ለህብረተሰቡ ለመድረስ የሪፎርም ሥራ ስለመጀመሩ አቶ ንጋቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡

አገልግሎት እሰጡ ያሉ ዘጠኝ ቅርንጫፍ ጣቢያዎች መኖራቸውን እና በአማካይ በእያንዳንዱ ቅርንጫፍ ከ3 እስከ 4 የአደጋ መቆጣጠሪያ ተሽከርካሪ ከበቂ ባለሙያ ጋር መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

አዲስ አበባ ካላት ስፋት እና ዕድገት አንጻር በአማካይ 27 ቅርንጫፍ ጣቢያዎች እንደሚስፈልጉ በቅርቡ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ያጠናው ጥናት ውጤት ማመላከቱ ይታወቃል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.