አፍሪካን ከተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ማግለል ኢፍትሐዊነት ነው- ሙሳ ፋኪ መሃመት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካን ከተባበሩት መንግስታት ደርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ማግለል ኢፍትሐዊነት ነው ሲሉ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃመት ገለጹ።
የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራትን ማዕከል ያደረገና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ እንዲሆን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ላይ የተደቀኑ ችግሮችንና ይዘዋቸውሊመጡ የሚችሉ ፈተናዎችን ቀድመን በመገንዘብ በጋራ ልናልፋቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡
የዋጋ ግሽበቱ ከሚጠበቀው በላይ ማሻቀብ፣ የነዳጅ ዋጋ መጨመርና ግጭት የአህጉሪቱ ተግዳሮቶች ሆነው መቀጠላቸውንም ተናግረዋል፡፡
ይህም የሀገራትን ኢኮኖሚ የሚያንኮታኩትና አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑን በመገንዘብ አማራጭ የመፍትሄ እርምጃ ማስቀመጥ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት እውን ለማድረግ ለንግድ ስራዎች በሚደረግ ጥበቃ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጣና እውን ለማድረግ መሰረተ ልማት፣ ኢነርጂኒና ዲጂታላይዜሽንን ማፋጠን የሚገባ ሲሆን ይህ ደግሞ ለነጻ ንግድ ቀጣናው እውን መሆን ዋነኛው መሰረት ነው ብለዋል፡፡
የሰዎችን በነጻነት የመዘዋወር መብት ማረጋገጥና በአለም አቀፍ መድረክ ያለንን አቋም በጋራ ማንጸባረቅ ከቻልን፣ እንዲሁም በትብበርና በአንድነት ከጸናን ድምጻችን ከፍ ብሎ ይሰማል ነው ያሉት፡፡
የአፍሪካ ህብረት በቡድን 20 ሀገራት ስብሰባ ላይ መካፈል እንዲችሉ እንዲሁም ህብረቱ ለአለም ችግር መቃለል ድምጹን እንዲያሰማ በጋራ ልንሰራ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በአህጉሪቱ የሚታዩ የፖለቲካና የደህንነት ችግሮች አሁንም ፈተና ሆነው መቀጠላቸውን በመጥቀስ ህገ መንግስታዊ ስርዓት በጣሰ መልኩ የሚደረጉ የመንግስታት ለውጦች ሀገራትን የመበታተን አደጋ እንደደቀነባቸው አመላተዋል፡፡
ሽብርተኝነትና ከምርጫ ውጭ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ጥረትና የአየር ጸባይ ለውጥ አሁንም የአህጉሪቱ ችግሮች ሆነው መቀጠላቸውን ጠቁመዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ግጭትን ለማስወገድ የሚረዱ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ በመናገር ለዚህ የሚረዱ ፕሮግራሞችንና ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ወደ ስራ ገብተናል ነው ያሉት፡፡
አፍሪካን በ2030 የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አህጉር ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ግባቸውን እንዲመቱ ህብረቱ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም መግለጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሊቀመንበሩ በኢትዮጵያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት እውን እንዲሆን ጥረት ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡