Fana: At a Speed of Life!

ተመድ ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስኬታማነት አብሮ ለመስራትና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው- አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

አዲስ አበባ፣ የካቲት11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስኬታማነት የበኩሉን ድጋፍና ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ።

በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ÷ አፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ብትሆንም እስካሁን በአግባቡ ለመጠቀም አልታደለችም ብለዋል።

አህጉሪቷ በተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች እየተፈተነች መሆኗን ጠቅሰው÷ ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና የጋራ ተጠቃሚነት በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

አፍሪካ እውን ለማድረግ የጀመረችው ነፃ የንግድ ቀጣና ትስስር ለአህጉሪቷ እመርታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል።

በአፍሪካና በሌሎችም የዓለም ክፍሎች በተለይም ታዳጊ አገራትን በመደገፍ ካሉባቸው ውስብስብ ችግሮች እንዲወጡ መስራት ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የዓለም የፋይናንስ ስርዓት ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ለአፍሪካና አጠቃላይ በማደግ ላይ ላሉ አገሮች በሚጠቅም መልኩ መቃኘት እንዳለበትም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ዓለምን እየፈተነ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ ችግር እልባት ለማበጀት የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለያዩ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እየተወያየ ያለው 36ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በነገው እለትም የሚቀጥል ይሆናል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.