ጠ/ሚ ዐቢይ ፓን አፍሪካኒዝምን የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እና በሰላማዊ አብሮ የመኖር ሐሳብ ሆኖ ማደግ እንዳለበት አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፓን አፍሪካኒዝም የትብብር ውሕደት ፣ የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እና በሰላማዊ አብሮ የመኖር ሐሳብ ሆኖ ማደግ እንዳለበት አሳስበዋል።
“ለተለዋዋጭ ዓለም ፓን አፍሪካኒዝምን መልሶ ማነቃቃት” በሚል ርዕስ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የመጀመሪያውን የፓን አፍሪካኒዝም ፎረም እያካሄደ ነው።
በፎረሙ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፥ በፓን አፍሪካ ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በቂ አይደሉም ፤ እንደ አህጉር ፓን አፍሪካኒዝምን በማቀንቀን ፈጣን ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ኢፕድ እንደዘገበው የፓን አፍሪካኒዝም ፎረም የፓን አፍሪካኒዝምን ሀሳቦች በማበልጸግ አፍሪካን በሁለንተናዊ ስርዓት ለማቆም ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።
አካዳሚው የፖሊሲና የምርምር ምክረ ሀሳቦችን ለማቅረብ፣ ብቁ አመራሮችን ለማፍራት ታስቦ የተቋቋመ እንደሆነና ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ፓን አፍሪካኒዝም የትብብር ውሕደት ፣ የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እና በሰላማዊ አብሮ የመኖር ሐሳብ ሆኖ ማደግ እንዳለበትም አሳስበዋል።