የሀገር ውስጥ ዜና

የዓለም ባንክ በ2023 ለአፍሪካ ከ50 ቢሊየን ዶላር የማያንስ በጀት እንደሚመድብ ተገለፀ

By Mikias Ayele

February 19, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ በ2023 ለአፍሪካ ከ50 ቢሊየን ዶላር የማያንስ በጀት እንደሚመድብ የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ኦስማኔ ዲያጋና ገለጹ።

በ36ተኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ኦስማኒ ዲያግና  እንደገለጹት÷ አፍሪካ ከምን ጊዜም በላይ ድጋፍ የሚያስፈልጋት ጊዜ አሁን ነው ።

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በድርቅ፣ በምግብ ዋስትና ፣ በኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖና በፖለቲካ አለመረጋጋት ፈተናዎች ውስጥ እንደምትገኝም ጠቅሰዋል።

ተፅዕኖው በመሪዎች በሳል የአመራር ስልትና በህዝቦች የጋራ ትብብር ብቻ እንደሚቀለበስ የጠቀሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ለዚህ የሚረዱ የመፍትሄ ሃሳቦችን ከአሁኑ ማመንጨት ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የዓለም ባንክ ችግሩን ለማቃለል ለአፍሪካ የሚያደርገው የፋይናንስ ድጋፍ በፈረንጆቹ 2022 ከነበረው በጀት ላቅ ያለ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

ባንኩ ከመደበኛ በጀቱ ውጪ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የሚደግፍ መሆኑን በማንሳት የአህጉሪቷ ህዝብና መንግስት ያላቸውን ሀብት በመጠቀም ይህን ከባድ ጊዜ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡