Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ እና የፓኪስታንን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ እየተሰራ ነው -አምባሳደር ጀማል በከር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የፓኪስታንን የንግድ ልውውጥ በ2023 ወደ 200 ሚሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው ሲሉ በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ተናገሩ፡፡

አምባሳደሩ ከፓኪስታኑ ደይሊ ታይምስ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት÷ ተቋማዊ ትስስር ባለመኖሩ ምክንያት የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነት ዝቅተኛ ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ይህንኑ በመገንዘብ ባለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያና በፓኪስታን መካከል ተቋማዊ ትስስርን ለመፍጠር ብሎም የመንግስታት እና የሀገራቱን የንግድ ሰዎች ግንኙነት ለማጠናከር ጥረቶች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ሀገራቱ አሁን ላይ በቱሪዝም ዘርፍ፣ በፖለቲካ ትብብር፣ በኢኮኖሚ ትስስር እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን  ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።

እስካሁን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ መጠን 78 ሚሊየን ዶላር መሆኑን የገለፁት አምባሳደሩ በ2023 መጨረሻ የሀገራቱን የንግድ ልውውጥ 200 ሚሊየን ዶላር ለማድረስ እቅድ መያዙን አመላክተዋል፡፡

ይህ የንግድ ትስስር እቅድም የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ገጽታ ሙሉ በሙሉ እንደሚለውጥ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ሩዝ፣ የመድሃኒት ምርቶች፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ የስፖርት እቃዎች እና የግንባታ ቁሳቁሶች ከፓኪስታን ወደ ኢትዮጵያ የሚላኩ ምርቶች መሆነው መለየታቸውንም ነው የሚገልጹት።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ በተለይም በግብርና፣ በግብርና ማቀነባበር፣ በማምረቻው እና በሌሎች ዘርፎች እምቅ አቅም እንዳላት አንስተዋል።

ከዚህ አንጻርም የፓኪስታን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ በመሰማራት እንደ ቡና፣ ሻይ፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና አትክልቶችን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡

አምባሳደሩ በቆይታቸው በኢትዮጵያ የዜጎችን ገቢ የሚያሻሽሉና ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን በመጥቀስ፥ ይህም በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱ ላይ የነበረውን ማነቆ በመቅረፍ በኩል ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.