Fana: At a Speed of Life!

ኮኬይን ዕፅ የያዘን ግለሰብ አስመልጠዋል ተብለው የተጠረጠሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ 27 ነጥብ 65 ኪሎ ግራም ኮኬይን ዕፅ የያዘን የውጭ ዜጋ አስመልጠዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኢንስፔክተሮች ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ፡፡

ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ በባለፈው ቀጠሮ የቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ እንዲሻሻልላቸው የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን÷ ዐቃቤ ህግ በክስ መቃወሚያ ጥያቄያቸውን በሚመለከት ክሱ ሊሻሻል እንደማይገባ ጠቅሶ ሁለት ገጽ መልስ በጽሁፍ ዛሬ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ የክስ መቃወሚያውን እና የዐቃቤ ህግን መልስ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለየካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዚሁ የክስ መዝገብ በ3ኛ እና በ4ኛ ተራ ቁጥር የተከሰሱ ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው የታዘዘ ሲሆን፥ 1ኛና 2ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት ግን ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ የታዘዙት ተከሳሾች የፌደራል ፖሊስ አባል የሆኑት ተጠርጣሪዎቹ 1ኛ ዋና ኢንስፔክተር አዲሱ ባሌማ እና 2ኛ ተከሳሽ ዋና ኢንስፔክተር ጌታነህ ሞገስ ናቸው።

1ኛና 2ኛ ተከሳሾች በአውሮፕላን ማረፊያ ቅርንጫፍ በቁጥጥር ስራ ላይ ተመድበው ሲሰሩ ታህሳስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 1:35 ላይ ከሳኦፓሎ በብራዚል ተነስቶ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ትራንዚት በማድረግ ወደ ጆሀንስበርግ የሚሄድ ብራዚላዊ ዜግነት ያለውን 4ኛ ተከሳሽ ክርስቲያን ዲ ኦሊቬራ በሻንጣው ውስጥ ከተያዘበት 27 ነጥብ 65 ኪሎ ግራም ኮኬይን ዕፅ ጋር ተረክበው በማግስቱ ቦሌ ሚሊኒዬም አዳራሽ አካባቢ በመውሰድ 3ኛ ተከሳሽ በሚያሽከረክረው ኮድ 3- B3 3259 አ.አ የሆነ ቪትስ መኪና ውስጥ በማስገባት ከእነዕፁ እንዲሸሽ አድርገዋል ተብለው ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል መከሰሳቸው ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.