Fana: At a Speed of Life!

ቻይና ዓለም አቀፋዊ ፀጥታና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ያለችውን ሠነድ ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ዓለም አቀፍ የፀጥታና ደኅንነት ኢኒሼቲቭ ያለችውን ሠነድ ዛሬ ይፋ አድርጋለች፡፡

ሠነዱ ይፋ የሆነው በሀገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በተዘጋጀ መድረክ ላይ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ፥ “ሠነዱ የዓለምን ሠላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ቻይና ያለባትን ኃላፊነት እና ለመወጣት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው” ብለዋል።

ዓለም አቀፋዊ ምኅዳሩ ሠላም ካልሆን የቻይና ዕድገት ዕውን እንደማይሆን ፤ የቻይና ደኅንነትም ካልተረጋገጠ ዓለም አቀፋዊ ፀጥታና ደኅንነት ሊረጋገጥ እንደማይችል ነው ያስረዱት፡፡

የቀረበው መነሻ ሠነድ ከ80 በላይ በሚሆኑ ሀገራት እና ቀጣናዎች ተቀባይነት ማግኘቱም ተመልክቷል፡፡

ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ደኅንነትን በመተባበር ማረጋገጥ የሚያስችሉ ጥልቅ ሐሳቦችም እንደተካተቱበት ፖለቲኮ ዘግቧል፡፡

ሠነዱ ቻይና በሩሲያ – ዩክሬን ጉዳይ ላይ አቋሟን በግልፅ ያንፀባረቀችበትና በሀገራቱ መካከል ያለውን ችግር መፍታት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ የመፍትሔ ሃሳብ ያመላከተችበት መሆኑ ነው የተገለፀው።

ዓለም አቀፋዊ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ከተቀመጡ መርኅዎች መካከል ፖለቲካዊ ውይይት እና ሠላማዊ ድርድር በቀዳሚነት ተጠቅሷል፡፡

ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድ መፍታት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ሠነዱ አመላክቷል፡፡

የሀገራትን ሉዓላዊነት ማክበር፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር ላይ ለተቀመጡት መርኅዎች መገዛት ፣ ሀገራት የደኅንነት ሥጋት ብለው የሚያቀርቧቸውን ሐሳቦች በአንክሮ መመልከት እና መፍታት ፣ በሀገራት መካከል የሚስተዋሉ የሐሳብ ልዩነቶችን በመወያየት መፍታት ፣ የዓለም ሀገራት ዓለም አቀፋዊ ደኅንነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆን ከቀረቡት የመርኅ ሐሳቦች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በመድረኩ ከ137 ሀገራት እና ቀጣናዎች የተውጣጡ አምባሳደሮች ፣ ዲፕሎማቶች ፣ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች እና ተወካዮች ተሳታፊ እንደሆኑም ተዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.