በጅምር ግንባታ ላይ ከነበረ ህንጻ ሶስት የቀን ሰራተኞች ወድቀው ህይወታቸው አለፈ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በአዲስ አበባ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በጅምር ግንባታ ላይ ከነበረ ህንጻ ሶስት የቀን ሰራተኞች ወድቀው ህይወታቸው አለፈ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ በስራ ላይ የነበሩት ሶስት ሰራተኞች ዛሬ 8 ሰዓት አካባቢ ላይ በጅምር ግንባታ ከነበረ ህንጻ ወድቀው ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡
በስራ ላይ የነበሩት የህንጻው ሰራተኞች በገመድ በተሰራ አሸዋና ሲሚንቶን ጨምሮ ሌሎች ዕቃዎችን በማያመላልሱበት ማውጫና ማውረጃ ጋሪ ላይ ሆነው ከ5ኛ ፎቅ ወደ ታች እየወረዱ በነበሩበት ወቅት ገመዱ ተበጥሶ መውደቃቸውንና ወዲያው ህይወታቸው ማለፉን ምክትል ኮማንደሩ ገልጸዋል።
ህይወታቸው ያለፈው ግለሰቦች ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 30 ዓመት የሚገመቱ ወጣቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የማቾች አስከሬን ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል መወሰዱንም ነው የገለጹት።
በታሪክ አዱኛ