Fana: At a Speed of Life!

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በጎንደር ከተማ ያስገነባው የዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በጎንደር ከተማ ያስገነባው የዳቦና ዱቄት ፋብሪካ በዛሬው ዕለት ተመርቋል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ እና የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ፋብሪካውን መርቀው ከፍተዋል።

የዳቦና የዱቄት ፋብሪካው በቀን 300 ሺህ ዳቦና 420 ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም እንዳለው ነው የተገለጸው፡፡

በ11 ወራት ውስጥ ግንባታው የተጠናቀቀው ፋብሪከው ከ100 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ሲሆን÷ ለ150 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩ ተመላክቷል፡፡

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች 12 የዳቦና የዱቄት ፋብሪካዎችን መገንባት አቅዶ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡

ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት ከጀመሩት መካከልም ዛሬ በጎንደር ከተማ የተመረቀው የዳቦና ዱቄት ፋብሪካ አምስተኛው ሲሆን ፥ እስካሁን በአዲስ አበባ፣ አጋሮ፣ ወላይታ ሶዶ እና ሐዋሳ ፋብሪካዎችን አስመርቋል።

ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ከተገነባው ፋብሪካ ውጪ ሁሉም ፋብሪካዎች ተመሳሳይ የማምረት አቅም እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡

በሌሎች ከተሞች ቀሪ ስድስት የዳቦና ዱቄት ፋብሪካዎች ግንባታ በመከናወን ላይ ሲሆን ፥ በቦንጋ ከተማ የሚገኘው ፋብሪካ በቅርብ ተመርቆ አገልግሎት እንደሚጀምር ተገልጿል።

የፋብሪካዎቹ ግንባታ የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር 11 መሰል ፋብሪካዎችን በጋራ ለመገንባት በተፈራረሙት መሰረት ተግባራዊ እየሆነ ነው ተብሏል።

ፋብሪካው በዋናነት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ የከተማዋ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የፕሮጀክቱ ቀዳሚ ዓላማ መሆኑም ተነስቷል።

በፍሬህይወት ሰፊው እና ምናለ አየነው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.