ዓለምአቀፋዊ ዜና

ኔቶ ለዩክሬን የጦር ጀቶች እንዳይቀርቡ ከለከለ

By Alemayehu Geremew

February 22, 2023

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 15 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት ለዩክሬን የጦር ጄቶች እንዳይቀርቡ ውሳኔ ማሳለፋቸው ተገለጸ፡፡

ምንም እንኳን ኪየቭ ምዕራባውያኑ ወዳጆቿን ደጋግማ ዘመናዊ የጦር ጀቶች እንዲልኩላት ብትወተውትም ሰሚ ጆሮ አላገኘችም ተብሏል፡፡

አንደ ፖላንድ እና ስሎቫኪያ ያሉ የኔቶ አባል ሀገራት በአንፃሩ ከምንም ይሻልሻል በሚል የቀድሞ ሶቪየት ሰራሽ ሚግ-29 ኤስ የተሠኙ ጀቶችን እንላክልሽ ብለዋል፡፡

የፖላንድ ፕሬዚዳንት አንድሬይ ዱዳ ÷ ከ50 ያነሱ ተዋጊ ጀቶች ብቻ እንደቀራቸው በመጥቀስ እንኳን ያላቸውን ጄቶች ለመሥጠት ለሀገራቸውም እንደማይበቃ ገልጸዋል።

ጣሊያንም ተዋጊ ጀቶችን ለኪየቭ እንደማታቀርብ አስረድታለች፡፡

ይልቁንም ኪየቭ ወታደራዊ ኃይሏን እንድታጠናክር ድጋፍ የሚሆናትን በርካታ ያረጁ አውሮፕላኖች ፣ ከፈረንሳይ ጋር በመተባበር ደግሞ የዓየር መቃወሚያዎችን እና ሚሳኤል ለመላክ ዝግጅት ላይ እንደሆነች አስታውቃለች፡፡

በትናንትናው ዕለት የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ጋር ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኋላ÷ “ሀገራት የራሳቸውን አቋም የመያዝ ነፃነት አላቸው” ሲሉ ቮሎድሚር ዜሌንስኪ መደመጣቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡