በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 6 ወራት ለ2 ሺህ 250 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሥድሥት ወራት ለ2 ሺህ 250 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ለታ አበበ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ባለሃብቶች በኦሮሚያ ክልል ያለውን እምቅ ሃብት በመጠቀም መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
በተለይም በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች ለኢንቨስትመንት ያለውን ምቹ ሁኔታ በማስተዋወቅ እና ቀልጣፋ አሰራር ከመዘርጋት አኳያ አመርቂ ውጤት መገኘቱን አንስተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም በርካታ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች መዋዕለ ንዋቸውን ለማፍፈስ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥም አስፈላጊውን መስፈርት ላሟሉ 2 ሺህ 250 ባለሃብቶች በተለያዩ ዘርፎች እንዲሰማሩ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ነው የገለጹት፡፡
በክልሉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ያሉት ምክትል ሃላፊው÷ በተለይም መሰረተ ልማትን ከማሟላት አንጻር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ስለሆነም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለ ሃብቶች በኦሮሚያ ያለውን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም በመረዳት መዋዕለ ንዋያቸው እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ