Fana: At a Speed of Life!

የዐባይ ሀገራት በዐባይ ውሃ ሀብት የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ስምምነት መድረስ አለባቸው – ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓባይ ሀገራት በዐባይ ውሃ ሀብት የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ስምምነት መድረስ እንደሚገባቸው የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሩ በኬኒያ ናይሮቢ ለ17ተኛ ጊዜ እየተከበረ በሚገኘው የዓባይ ቀን ኢትዮጵያን በመወከል ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግራቸውም ፥ የዓባይ አባል ሀገራት እየጨመረ የመጣውን የህዝብ የውሃ ፍላጎት እየቀነሰ ከሚገኘው የውሃ ሀብት ጋር ለማጣጣም  ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የዓባይ አባል ሀገራት የልማት ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ ÷ የአባል ሀገራቱ የልማት ፍላጎት በዋናነት የምግብ ዋስትና፣ የመብራት አቅርቦትና የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽነት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

እነዚህን ፍላጎቶች ማሟላት የሚቻለው በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የጋራ ተጠቃሚነት ስምምነት ላይ መድረስ ሲቻልና የጋራ የሆነውን የውሃ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ከተሰራ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡

የዓባይ አባል ሀገራት ውስን የሆነውን የውሃ ሀብት ለመጠቀም ለትብብር ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው የጠየቁት ሚኒስትሩ ፥ ሀገራቱ የዓባይ የትብብር ማዕቀፍን ሊያፀድቁ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

የዓባይ ቀን ለ17ተኛ ጊዜ በኬኒያ ናይሮቢ ‘‘በናይል ትብብር ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ልማት’’ በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.