ሩሲያ ከቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ጋር ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ ጀመረች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የሦስትዮሽ ወታደራዊ የባህር ኃይል ልምምድ ማድረግ ጀመሩ።
‘‘ሞሲ ሁለት’’ ተብሎ የተሰየመው ወታደራዊ የባህር ኃይል ልምምድ በደቡብ አፍሪካ ህንድ ውቅያኖስ መካሄድ መጀመሩም ነው የተገለጸው፡፡
በልምምዱ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳን ጨምሮ የሩሲያ የባህር ኃይል አዛዥ ኒኮላይ ይቭምኖቭ እና ሌሎች የሀገራቱ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
የሩሲያ የባህር ኃይል አዛዥ ኒኮላይ ይቭምኖቭ በመክፈቻው ሥነ-ስርዓት ላይ ፥ በሦስቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት የጠበቀ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ልምምዱ የዓለምን ውቅያኖሶች ደህንነትን ለማረጋገጥና በባህር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችንና ስጋቶችን ቀድሞ ለመከላከል ያለመና የባህር ኃይል ትብብርን ለማጠናከር በሀጋረቱ መካከል ያለውን ጥልቅ ፍላጎት አመላካች ነው ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ በልምምዱ ቢያንስ 350 የደቡብ አፍሪካ የባህር ኃይል እና ሌሎች ወታደራዊ አባላት አሳትፋለሁ ብላለች፡፡
የአሁኑ የሀገራቱ የባህር ሃይል ወታደራዊ ልምምድ ከ2019 ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ የሚደረግ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የደቡብ አፍሪካ መከላከያ ሃይል የሀገሪቷን ደህንነት አደጋ ላይ ከሚጥሉ አካላት በመጠበቅ እያስከበረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ናቸው፡፡
በልምምዱ ላይ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎችን የታጠቁ መርከቦችን ጨምሮ ወታደራዊና የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ መርከቦች ተሳታፊ መሆናቸውን አፍሪካ ኒውስ በዘገባው አመላክቷል።