በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው የወጣቶች የአዕምሮ ህመም ተጋላጭነት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በወጣቶች ዘንድ የሚስተዋለው የአምሮ ህመም በመላው ዓለም እየጨመረ በመምጣት ላይ የሚገኝ የጤና ቀውስ ስለመሆኑ የዓለም ሳይካትሪስት ማህበር ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመተ ላይ ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።
ይህ ቀውስ በተለይም ደግሞ ከዲጂታል ምህዳር መስፋት ጋር ተያይዞ እየተባባሰ መምጣቱን ነው ሪፖርቱ የሚያመለክተው።
አሁን ላይ ወጣቶች ግንኙነት የሚያደርጉት የማህበራዊ ትስስር ገፆችን በመጠቀም መሆኑ አንዱ ተጋላጭነታቸውን ያሰፋ ጉዳይ ስለመሆኑ ይኸው ሪፖርት ይጠቅሳል።
ሪፖርቱ በወጣቶች ዙሪያ በርካታ አካላዊ እና ማህበራዊ የሆኑ ለአዕምሮ ህመም የሚያጋልጡ ነገሮች መኖራቸውን ያነሳል።
በኢትዮጵያ የወጣቶች የአዕምሮ ህመም ተጋላጭነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል።
በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ የአዕምሮ ሆስፒታል የምርምር እና ስልጠና ዳይሬክተር አቶ ዘገየ ዮሐንስ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ በአፍላ እድሜ የሚገኙ ወጣቶች የአዕምሮ ህመም ተጋላጭነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡
በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በአለም ላይ 29 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች ለአዕምሮ ህመም ተጋላጭ ሲሆኑ፥ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ወጣቶች 12 በመቶ ያክሉ የአዕምሮ ህመም ተጋላጭ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ለወጣቶች የአዕምሮ ህመም በዚህ መጠን መስፋፋት የተለያዩ ምክንያቶች ቢጠቀሱም የወጣት ዜጎቸ የሱስ ተጋላጭነት ከፍተኛውን ስፍራ እንደሚይዝ ጠቁመዋል፡፡
ከሱስ በተጨማሪ በዘር ምክንያት ፣በወጣትነት ጊዜ በሚፈጠሩ የሆርሞን መቀያየሮች እንዲሁም የተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች ለአዕምሮ ህመም አጋላጭ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አምራች ወጣቶች ለአዕምሮ ህመም መጋለጣቸው የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችን እንደሚያስከትል የገለፁት ባለሙያው፥ ችግሩን ለመግታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይገባል ይላሉ።
በመንግስት በኩል የወጣቶችን የስብዕና ግንባታ ማስፋፋት፣የሐይማኖት ተቋማት ወጣቶች በጥሩ ሰብዕና እንዲገነቡ ማድረግ እንዲሁም ቤተሰብ ልጆችን በስነ ስርዓት እንዲያድጉ ማድረግ ይገባል ሲሉ መክረዋል።
የአዕምሮ ህመምን በህክምና ብቻ መከላከል እንደማይቻል ያስረዱት ዳሬክተሩ ከአዕምሮ ህክምና ተቋማት በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች እና ከላይ የተጠቀሱ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ባይ ናቸው።
በሚኪያስ አየለ