የአውሮፓ ህብረት በጤናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት በፋይናንስ፣ በልምድ ልውውጥና በሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት በኩል ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ለመስራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባልና የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተወካይ ዶ/ር አብዱልሰመድ ሁሴን በካትሪና ቫን ብረምፕት የተመራውን የአውሮፓ ህብረት አባላት ልዑካን ቡድንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል በተለይም በእናቶች እና ሕፃናት፣ በአቅም ግንባታ፣ በልምድ ልውውጥ እና በሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ከኅብረቱ ጋር በጋራ እንደምትሰራ ዶ/ር አብዱልሰመድ አብራርተዋል።
የአባላቱ ተወካይ ካትሪና ብረምፕት በበኩላቸው ፥ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻልና በዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
አክለውም ፥ የህብረቱ አባላት የመጡበት አንዱ ዓላማም፤ በትብብር ላይ ተመስርተን በሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ላይ የሚያጋጥሙ የጤና ተግዳሮቶችን ለመፍታት ነው ብለዋል።
ህብረቱም በፋይናንስ፣ በልምድ ልውውጥና በሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት በኩል ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል፡፡
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ተጎጂ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች በጥናት ላይ የተመሠረተ እገዛ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገነነው መረጃ ያመለክታል፡፡