የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመሰረተ ልማት ችግር ለቱሪዝም ዘርፉ ማነቆ እንደሆነበት ገለፀ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በመህስብ ስፍራዎች የታደለ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ከቱሪዝም ዘርፍ ገቢ እንዳያገኝ የመሰረተ ልማትና የጎብኚዎች ማረፊያ ቦታዎች አለመኖር ማነቆ እንደሆነበት ገለፀ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ፥ ክልሉ በታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች የበለፀገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክልሉ በውስጡ በርካታ ብርቅዬ እስሳትን የያዘው የጨበራ ጩርጩራ እና የኦሞ ብሄራዊ ፓርኮች ባለቤት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በዚሁ በኦሞ ብሄራዊ ፓርክም ውድምቢ የተባለችና በኢትዮጵያ ብቻ የምትገኝ አጥቢ እንስሳት እንደምትገኝም ነው የተናገሩት፡፡
እንዲሁም በዩኔስኮ የተመዘገቡትን የካፋና ሻካ ዞን ጥብቅ ደኖችን ጨምሮ በጉራፈርዳና ሌሎች አካባቢዎች ጥብቅ ደኖች እንዳሉም አስረድተዋል።
በዚህም የክልሉን የጎብኚ መዳረሻ ስፍራዎች ከማልማትና ለጎብኚ ምቹ ከማድረግ አንፃር በክልሉ መንግስት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም ክልሉ ያሉትን ሀብቶች ከማስተዋወቅ አንፃር የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም ዘጋቢ ፊልምን ጨምሮ የተለያዩ የማስተዋወቅ ስራዎች መሰራታቸውን እና እየተሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ የሚገኙትን ጥብቅ ደኖች ባሉበት ለማቆየት ህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ የራሱን ሃብት እንዲጠብቅ ስራዎች መሰራታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ክልሉ በሚፈለገው ልክ ከቱሪዝም ሀብቶቹ ገቢ እንዳያገኝ የመሰረተ ልማት እና የጎብኚዎች ማረፊያ ቦታዎች አለመኖር ፈተና እንደሆነበትም ጠቅሰዋል።
ይህን ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ በራስ አቅም በአንዳንድ ቦታዎች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ግን በቂ አለመሆኑን አንስተዋል።
እንደ ሆቴል እና ሎጅ የመሳሰሉ የጎብኚዎች ማረፊያ ቦታዎችን ከማልማት አንፃርም የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዚህም ዘርፍ ለመሰማራት የሚመጡትን ባለሃብቶች ክልሉ በተለየ መልኩ እንደሚያበረታታ እና እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ክልሉ ከቱሪዝም ዘርፍ 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ለማግኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑን እና ባለፉት ስድስት ወራት 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ማግኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው