Fana: At a Speed of Life!

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመሥራት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ።

ስምምነቱን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው እና የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገናነው ጐፌ ተፈራርመዋል።

የሥምምነት ሠነዱ በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ በየዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት፣ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ወደ ተግባር ለመቀየር እና የማኅበረሰብ ሕይወትን ለመለወጥ በትብብር መሥራት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በተጨማሪም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ለሁለንተናዊ ሀገራዊ ዕድገት በጋራ ይሠራሉ ፣ በዩኒቨርሲቲው የሚከናወኑ ማኅበረሰብ ተኮር ጉዳዮችንም በሚዲያ ተደራሽ ለማድረግ ይተባበራሉ ተብሏል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ወቅታዊ፣ አዝናኝ ፣ አስተማሪ ፣ ለኅብረተሰቡ ሕይወት ቅርብ የሆኑ፣ ለውጥ የሚያመጡ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ መረጃዎችን በኤፍ ኤም ጣቢያዎቹ፣ በሀገር አቀፍ የሬዲዮ ስርጭት፣ በቴሌቪዥን እና በዲጂታል ሚዲያ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ቋንዎች በፍጥነትና በጥራት የሚያደርስ በመሆኑ ይህ አቅም ለዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሆን አቶ አድማሱ ዳምጠው በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲዉ በተማሪዎች አገልግሎት፣ በትምህርት ልኅቀት፣ በማኅበረሰብ ዓቀፍ የልማት ሥራዎች እና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ሥራዎች የሚያስተዋውቅበት ምኅዳር እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ፋና የብቁ ባለሙያዎች ሚዲያ መሆኑን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፥ በማኅበረሰብ ሬዲዮ ዘርፍ ፋና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ፣ የስልጤ ማኅበረሰብ እና የአርጎባን ገንብቶ ያቋቋመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሌሎች ተቋማትን የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ግንባታም ለማከናወን ተቋሙ በሥራ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ፋና በሚሰራቸው የምርምርና የሥልጠና ዘርፎችም፥ ከሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተቀናጅቶ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገናነው ጐፌ በበኩላቸው፥ ተቋማቸው ከፋና ጋር በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱንና በቀጣይም ኅብረተሰብ ተኮር ሥራዎችን በጋራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር የዩንቨርሲቲውን ገፅታ ለኅብረተሰቡ ለማስተዋወቅ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

የጋራ ስምምነቱ ሁለቱን ተቋማት ይበልጥ የሚያቀራርብ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.