Fana: At a Speed of Life!

በ2 ቢሊየን ብር ወጪ የተጀመረው የቦሌ አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ ከተቋረጠ ከአራት አመት በላይ ሆኖታል 

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 17 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በ2 ቢሊየን ብር ወጪ የተጀመረው የቦሌ አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ ከተቋረጠ ከአራት አመት በላይ እንደሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባደረገው ምልከታ አረጋግጧል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሆስፒታሉ ግንባታ በሚካሄድበት አካባቢ ባደረገው ምልከታ በአሁኑ ወቅት ለሆስፒታሉ ግንባታ የሚውሉ ብረቶች ለዝገትና ለብክነት መጋለጣቸውን መታዘብ ችሏል።

በወቅቱ የሆስፒታሉ የቦታ ርክክብ ሲደረግ በህጋዊ ውል አለመታሰሩንም በማስረጃ ማረጋገጥ ተችሏል።

ለፕሮጀክቱ በ2009 ዓ.ም በቀድሞው የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ እና በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አመራሮች መካከል የ3 ነጥብ 98 ሔክታር ቦታ ርክክብ መደረጉን የተገኘው ማስረጃ ያመላክታል።

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽህፈት ቤት የለማ መሬት ማስተላለፍ ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ ተስፋዬ፥ በወቅቱ ህጋዊ ውል ሳይታሰር “ፖለቲካዊ ውሳኔ” በሚል በአመራሮች መካከል ብቻ የቦታ ርክክብ መደረጉን አስታውሰዋል።

ከቦታ ርክክቡ በኋላም የሆስፒታሉ ግንባታ በ2009 ዓ.ም ተጀምሮ መቋረጡን ጠቅሰዋል።

ግንባታው ከተቋረጠ ማለትም ከለውጡ በኋላ  ሰኔ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ስለይዞታው የከተማ አስተዳደሩ ተጠይቆ በጉዳዩ ዙሪያ ምንም አይነት የተሟላ መረጃ እንደሌለው መልስ መስጠቱ  ተጠቅሶ፥ አጠቃላይ በግንባታው ዙሪያ በካቢኔ የተሰጠውን ውሳኔ ጨምሮ  አስፈላጊው መረጃ ይሰጠን የሚል የትብብር ደብዳቤ በአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ፊርማ ያረፈበት ጥያቄ መቅረቡንም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያገኘው ማስረጃ ያመላክታል።

በለውጡ ወቅት ሆስፒታሉን ለመገንባት ስምምነት የገባው ተቋራጭ ግንባታውን አቋርጦ ጥሎ ወደ ውጭ ሀገር መውጣቱን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ተናግረዋል።

ተቋራጩን በህግ የመጠየቁ ሂደት እንዳለ የጠቀሱት ኃላፊው በአሁኑ ወቅት የሜጋ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተረክቦ ጥናትና ልየታ በማድረግ ለግንባታ ጨረታ ለማውጣት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እየሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።

ግንባታው ከአራት አመት በላይ መዘግየቱን ተከትሎ እና በወቅቱ የነበረው የግንባታ ግብዓት ዋጋና አሁን ያለው ዋጋ ልዩነት እንዳለው ያነሱት ኃላፊው፥ በዚህ ምክንያት መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ እንደሚዳርገው አንስተዋል።

ከኮንስትራክሽን ቢሮ ፕሮጀክቱን የተረከበው የሜጋ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደቦ ቱንቃ በበኩላቸው፥ የሆስፒታሉ ግንባታ ውል በተቋራጩ እጅ መቆየቱን ተከትሎ እንደ አዲስ ግንባታው የሚፈልገውን ሂደት ለማስጠናት በማስፈለጉ ምክንያት ወደ ግንባታ ለመግባት ጊዜ መውሰዱን ገልጸዋል።

ከሁለት አመት በፊት የሜጋ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት መቋቋሙን ተከትሎ የሆስፒታሉን ፕሮጀክት በዚህ በያዝነው በጀት አመት ስድስት ወራት ውስጥ ተረክበው የሚቀነሱና የሚስተካከሉት እንደ አዲስ ማስጠናታቸውንም ነው የተናገሩት።

ፕሮጀክቱም በቀጣይ አንድ ወር ግልጽ ጨረታ ወጥቶበት የሆስፒታሉ ግንባታ እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.