በኦሮሚያ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የእለት ደራሽ እርዳታ እየቀረበ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ10 ዞኖች በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የእለት ደራሽ እርዳታ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ሀላፊ አቶ ሙስጠፋ ከድር በክልሉ የተከሰተውን ድርቅና እተደረገ ያለውን ድጋፍ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በክልሉ ደቡብ ምስራቅ አካባቢ ላለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ በአምስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ሳይዘንብ መቅረቱን ገልጸዋል።
“የድርቁ ሁኔታ እየተባባሰ በመምጣቱ ቀደም ብሎ በ8 ዞኖች 3 ነጥብ 2 ሚሊየን የነበረው የእርዳታ ፈላጊ ዜጎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት በ10 ዞኖች ወደ 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ከፍ ብሏል” ብለዋል።
ለእነዚህ ዜጎች የክልሉ መንግስት ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን 8 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የምግብ እህል እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ ተደራሽ ማድረጉንም ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘገቧል።
አቶ ሙስጠፋ እንዳሉት በአካባቢው በጠቅላላ 102 የውሃ ቦቴዎች ለሰውና ለእንስሳት ውሃ እያቀረቡ ሲሆን ለእንስሳት መኖ የሚውል ከ186 ሺህ በላይ እስር ሣርም ቀርቧል።
በቦረና ዞን ብቻ ለ867 ሺህ ሰዎች የእለት ደራሽ እርዳታ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ባለፉት ወራት 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚገመት 465 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል መቅረቡንም ሃላፊው ተናግረዋል።
“እርዳታ ለማስገባት አመቺ ባልሆኑ የዞኑ አካባቢዎችም 600 ሚሊየን ብር ጥሬ ገንዘብ ተከፋፍሏል” ብለዋል።
እንደ አቶ ሙስጠፋ ገለጻ በዞኑ 27 ቦቴዎች ውሃ እያቀረቡ ሲሆን በተለያየ ምክንያት አገልግሎት ያቆሙ የውሃ ተቋማትም መልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ በጥገና ላይ ናቸው።
የድርቁ ሁኔታ ሊበረታ ስለሚችል በቀጣይ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ አቶ ሙስጠፋ ጥሪ አቅርበዋል።