ዶ/ር ግርማ አመንቴ በደቡብ ክልል በበጋ መስኖ የለማ የስንዴ ማሳን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ በጎፍለላ ቀበሌ በበጋ መስኖ እየለማ የሚገኝ የስንዴ ማሳን ጎብኝተዋል፡፡
በደቡብ ክልል በተያዘው የምርት ዘመን ከ13ሺህ 400 ሄክታር መሬት በላይ ስንዴ በበጋ መስኖ እየለማ መሆኑ ተጠቁሟል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ748 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
በስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ በጎፍለላ ቀበሌ በበጋ መስኖ እየለማ ያለው መሬት አብዛኛው ከስደት ተመላሽ በሆኑ ወጣቶች የለማ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በክልሉ በበጋ መስኖ ልማት ከ 4 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በጉብኝት መርሐ-ግብሩ በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ፣ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።