አቶ አህመድ ሽዴ ከቻይና ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከቻይና ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴንግ ሊ ኤል ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ባለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል፡፡
አቶ አሕመድ ሽዴ÷ ኢትዮጵያ እና ቻይና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን መሰረት ያደረገ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንዳላቸው አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ትብብር ለማሳደግ ቁርጠኛ ናት ያሉት ሚኒስትሩ÷ በቀጣይ ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማስመዝገብ የሀገራቱን ግንኙነት ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ዴንግ ሊ ኤል በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ ሚና የምትጫወት ቁልፍ እና ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኗን አውስተዋል፡፡
ሀገራቸው በቻይና-አፍሪካ ትብብር መድረክ እና በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ማዕቀፍ ግንኙነቷን የበለጠ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት መናገራቸውን በቻይና ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የቻይና መንግሥት የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ ጋር የረጅም ጊዜ ጠንካራ አጋርነት እንዳለውም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡