የተማሪዎች ውጤት እንዲጎለብት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተመለከተ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ቢ ሲ) የተማሪዎች ውጤት እንዲጎለብት በትኩረት መስራት እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ፡፡
በክልሉ በሀገር አቀፍ የ12ተኛ ክፍል ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት አሰጣጥ ሥነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡
አቶ ኦርዲን በድሪ በመድረኩ እንደተናገሩት÷ በዘንድሮው ሀገር አቀፍ የ12ተኛ ክፍል ፈተና እንደ ክልል አበረታች ውጤት ቢመዘገብም አጥጋቢ አይደለም፡፡
በመሆኑም የተማሪዎችን ውጤት ለማጎልበት የበለጠ መስራት ያስፈልጋል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ትኩረታቸውን በትምህርታቸው ላይ በማድረግ ለበለጠ ውጤት መትጋት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙክታር ሳሊህ÷ በ2014 ሀገር አቀፍ ፈተና ክልሉ 10 ነጥብ 5 በመቶ ተማሪዎችን ማሳለፉን ተናግረዋል፡፡
በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የዋንጫ፣ የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።