በቀሪ የበጀት ዓመቱ ወራት የከተማዋን ህዝብ ኑሮ የሚያቀሉ ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት ይሰራል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀሪ የበጀት ዓመቱ ወራት የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብን ኑሮ የሚያቀሉ ፕሮጀክቶች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው የማጠቃለያ ንግግርና የስራ አቅጣጫ የሰጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፥ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ጫናን በመቀነስ የነዋሪውን ችግር እንዲያቀሉ የተጀመሩት የእሁድ ገበያ እና የሌማት ትሩፋት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
በተለይም በእሁድ ገበያ መሰረታዊ ፍጆታ የሆኑ ምርቶች በቀላሉ ህብረተሰቡ ጋር እንዲደርሱ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በቀሪ የበጀት ዓመቱ ወራት ያልተከናወኑ ተግባራት ተለይተው በእቅድ ክለሳ እንዲካተቱ በማድረግ የህዝቡን ኑሮ የሚያቀሉ ፕሮጀክቶች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰሩም ከንቲባዋ አክለው ገልጸዋል፡፡
አስተዳደሩ ከተማዋን ለነዋሪዎችዋ ጽዱ ውብና ምቹ ከማድረግ ባሻገር ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ከተማነትዋን የምትመጥን ለማድረግ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ተግባራዊ እያደረገ ነውም ብለዋል፡፡
አገልግሎት አሰጣጥን ከወቅቱ ጋር እንዲሄድ ለማስቻልም በርካታ ዘርፎችን የማዘመንና የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ከንቲባዋ አክለውም ፥ በመዲናዋ ባለፉት ስድስት ወራት ከ200 በላይ አመራርና ሰራተኞች ላይ የብልሹ አሰራርና ሌብነት ክስ መመስረቱንም አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል ወደ ከተማዋ የሚደረገውን ፍልሰትና በህቡእ አደረጃጀት የሚደረግ ህገወጥነት ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ማለታቸውን ከከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡