ቴክ

የሽመና ሥራ ምርታማነትን ከ300 በመቶ በላይ ያሳደገው ቴክኖሎጂ

By ዮሐንስ ደርበው

February 27, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽመና ሥራን በማቅለል ምርታማነትን ከ300 በመቶ በላይ ያሳደገው በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ አውቶማቲክ መሸመኛ ማሽን በሀገር ልጆች ተመርቶ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡

ቴክኖሎጂው የበለጸገው አዲስ አበባ በሚገኘው ‹ሚርካ ኢንጂነሪንግ የግል ኢንተርፕራይዝ› መሆኑን የኢንተር ፕራይዙ ባለቤት ኢንጂነር ቻላቸው ሰጠኝ ይናገራሉ፡፡

ያበለጸጓቸው የፈጠራ ሥራዎችም የክር (የድርና ማግ) ማጠንጠኛ እና አውቶማቲክ መሸመኛ ማሽኖች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

አውቶማቲክ የመሸመኛ ማሽኑ የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም የተለያዩ ባህላዊና ዘመናዊ ልብሶችን ያመርታል ሲሉ አገልግሎቱን ያስረዳሉ፡፡

ቴክኖሎጂዎቹ በአብዛኛው በራስ ፈጠራ መሠራታቸውን እና ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በመሻሻል ላይ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል፡፡

ከምርታማነት አኳያ የማጠንጠኛ ማሽኑ እስከ 600 በመቶ ምርታማነትን ይጨምራል ነው ያሉት፡፡

አውቶማቲክ መሸመኛ ማሽኑም ከ300 እስከ 1 ሺህ በመቶ ምርታማነትን እንደሚጨምር የፈጠራ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

ኢንጂነር ቻላቸው ስለ ፈጠራ ሥራዎቹ ጠቀሜታ ሲናገሩ÷ በተለይም አውቶማቲክ የመሸመኛ ማሽኑ በሞተር ስለሚንቀሳቀስ ጊዜና ጉልበትን በመቆጠብ እና በሰዓት በአማካይ ከ5 እስከ 9 ሜትር ልብስ በማምረት ጥቅሙ የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ እና የሴቶችን የሥራ ጫና በመቀነስ፣ ለዘመናት በሰው ኃይል የታጠረውን የሽመና አሠራር በቴክኖሎጂ በመተካት ረገድ ፋይዳው የጎላ ስለመሆኑም ነው የሚናገሩት።

ለአሠራር ምቹ መሆኑና ለሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር የራሱን አስተዋጽዖ እንደሚያበረክትም አስረድተዋል፡፡

የፈጠራ ሥራዎቹም በተመጣጣኝ ዋጋ ገበያ ላይ ውለው አገልግሎት እየሰጡ ስለመሆኑም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣንም ለፈጠራ ባለሙያው ሥራዎች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡

እንዲሁም የፈጠራ ሥራዎቹ ተጨማሪ ማሻሻያ ተደርጎባቸው ለባለስልጣኑ ቀርበው በሂደት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!