ዓለምአቀፋዊ ዜና

ትናንት በጣሊያን በሰጠመችው ጀልባ ከ100 በላይ ሰዎች ለህልፈት ሳይዳረጉ እንዳልቀረ ተነገረ

By Tamrat Bishaw

February 27, 2023

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ትናንት በደቡባዊ ጣሊያን ባህር ላይ በሰጠመችው የስደተኞች ጀልባ ህጻናትን ጨምሮ ከ100 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ሳያልፍ አይቀርም የሚል ስጋት መኖሩ ተገለጸ።

እስካሁን ቢያንስ 62 ስደተኞች ህይወታቸው ማለፉ የተረጋገጠ ሲሆን አንድ ጨቅላ ህጻንን ጨምሮ 12 ህጻናትም ከሟቾች መካከል ይገኙበታል ተብሏል።

ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎችን አሳፍራ የነበረችው ጀልባ እሁድ እለት ክሮቶኒ አቅራቢያ ለማረፍ ስትሞክር መሰበሯ ተነግሯል።

የአፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ሶማሊያ፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ እና ኢራን ዜጎች በጀልባ ላይ እነደነበሩም ተገልጿል።

በካላብሪያ ክልል አቅራቢያ በሚገኝ የባህር ዳርቻ የስደተኞቹ አስከሬን መገኘታቸውም ነው የተጠቆመው።

የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች እንዳሉት እስካሁን 80 ሰዎችን በህይወት ማግኘት ተችሏል። አንድ በህይወት የተረፈ ግለሰብም ከህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋሉን ቢቢሲ ዘግቧል።