Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል መላው አፍሪካውያን ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ያነሳሳ ነው – የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢኮኖሚ አማካሪ ዮሴፍ ሜንሳህ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 20 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን በወራሪው ጣሊያን ላይ በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገቡት ድል መላው አፍሪካውያን ቅኝ ግዛትን እንዲታገሉ ያነሳሳ እንደነበር የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢኮኖሚ አማካሪ ዮሴፍ አታ ሜንሳህ ገለጹ።

አማካሪው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ የዓድዋ ድል፥ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት አገዛዝ ነጻ ለመውጣት በሚያደርጉት ትግል ድፍረትን ያላበሰ እና ያነሳሳ እንደነበርም ነው የተናገሩት።

የአፍሪካ ሀገራትም በኢትዮጵያ ድል መነሻነት ከቅኝ ገዥዎች እና ኢምፔሪያሊስት ሃይሎች ጋር የነጻነት ትግል መጀመራቸውንም አስረድተዋል።

ጋና በቀድሞ መሪዋ ኩዋሜ ንክሩማ አማካኝነት ነፃነታቸውን ካረጋገጡ ሀገራት ተርታ ልትሠለፍ የቻለችው በወቅቱ የቅርብ ጓደኛቸው ከነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ-ሥላሴ ድጋፍ ስለነበራቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢኮኖሚ አማካሪው ጋና በግርማዊነታቸው ድጋፍ ከእንግሊዝ የአገዛዝ ቀንበር ነፃ የወጣችበት አጋጣሚ የጋናን ብቻ ሳይሆን አፍሪካ በመሪዎቿ ነፃ መውጣቷን አመላካች መሆኑንም አንስተዋል።

የወቅቱ የኢትዮጵያ ድል አፍሪካውያን በአስተሳሰብም የላቀ ማሰብ እንደሚችሉ ያሳየ ብሎም የራሳቸውን ችግር በራሳቸው የመፍታት ዐቅም እንዳላቸው ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

ድሉ የዓለምን አስተሳሰብ የቀየረና በአምባገነንነት የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ ሲባዝኑ የነበሩትን የውጪ ወራሪ ኃይሎችን ጉዞ በመግታት ለፓን አፍሪካኒዝም ዕሳቤ መወለድ ቁልፍ እንደነበርም ነው ያስረዱት።

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አማካሪ የሆኑት ጆሴፍ አታ ሜንሳህ የዓድዋ ድል የሁሉም አፍሪካውያን ድል መሆኑንም አውስተዋል።

ድሉ ለአፍሪካ ምልክት መሆን እንደቻለና በርካታ አፍሪካውያንም ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ያነሳሳ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

በዮናታን ዮሴፍ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.